ዝግመተ ለውጥ — የዘመኑ ሳይንስ ቱሩፋት? ወይስ ዘመናትን ያስቆጠረ ፍልስፍና?
የፍጥረትን አመጣጥ በተመለከተ ሰዎች ለዘመናት ሲያነሱት እንዲሁም መልስ ሊሰጡበት የሞከሩት ጥያቄ ነው። ይህ ጥያቄ ትንሹንና ትልቁን፣ ኋላ ቀሩንና የሰለጠነውን ማህበረሰብ በማስጨነቅ አንድ ያደረገ ጉዳይ ነው። ለዚህ ምላሽ መስጠት መቻል ደግሞ እፎይታን የሚሰጥ በመሆኑ፣ የፍልስፍና አስተማሪዎችና የሥነ-ፍጥረት አጥኚዎች ምላሽ ለመስጠት ራሳቸውን በማስጨነቅ ሲጠብቡ ኖረዋል።
የዝግመተ ለውጥ አስተሳሰብ በጥንት ሥልጣኔዎች
ዛሬ ላይ እንደ አዲስ መስለው በዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ወይም በአጠቃላይ የሕዋ አመጣጥ ዙሪያ የሚሰጡ ‘ሳይንሳዊ’ ትንተናዎች ላይ የተቀመጡት ሐሳቦች፤ ምንም እንኳን የዘመኑ የምርምር ውጤቶች ቢመስሉም፣ እነዚህ አመለካከቶች ሲንጸባረቁ ከቆዩ ግን ሺህ ዓመታትን አስቆጥረዋል። ይህ ደግሞ እየቀረቡልን ስላሉት ትንታኔዎች መነሻቸው ፍልስፍና ወይስ መረጃ ወይስ ሌላ ነገር ብለን እንድንጠይቅ ሊያደርገን ይችላል።
በታሪክ የተነሱ ታላላቅ ስልጣኔዎችን ስንመለከት፣ ለዚሁ ጥያቄ ምላሽን ለማግኘት ፍልስፍናን በተንተራሱ ምርምሮች አበክረው ይፈልጉና ይሞክሩ ነበር። በጥንቷ ግሪክ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ሌሎች ሥልጣኔዎች ውስጥ የነበሩ ፈላስፋዎችና አሳቢዎች ስለ ዓለም አመጣጥ፣ የሕይወት ትርጉም እና የሰው ልጅ ቦታ በዩኒቨርስ ውስጥ ለመረዳት ብዙ ንድፈ ሐሳቦችንና ማብራሪያዎችን አስቀምጠዋል።
“ቀደምት ፈላስፎች ዝግመተ ለውጥ ላይ ላጠነጠነ ግምታዊ አስተሳሰብ ቦታ ይሰጡ ነበር።”1
መዛግብትን ወደኋላ መለስ ብለን ካየን የዝግመተ ለውጥ ሀሳብ ትንተናው ወደ ሳይንስ ዘርፍ ከመምጣቱ በፊት መነሻው ከፍልስፍናው አለም ነበር። በተለይም የሩቅ ምስራቅ እንዲሁም የግሪክ ፈላስፎች በዚህ ዙርያ ዛሬ ላይ ካለው የዝግመተ ለውጥ ትንተና ጋር በመሰረትዊ ሃሳቡ ተመሳሳይ የሆነ ትንተና ይሰጡ ነበር።
የዝግመተ ለውጥ አስተሳሰብ፣ ማለትም ዝርያዎች በረጅም ጊዜ በሆነ አዝጋሚ የለውጥ ሂደት ይለወጣሉ የሚለው አመለካከት፣ የዘመናችን ሳይንስ ግኝት ብቻ አይደለም። ይህ ጽንሰ ሐሳብ በጥንት ግሪካውያን፣ ሮማውያን፣ ቻይናውያን እና በመካከለኛው ዘመን በተነሳው የእስልምና ሳይንስ ውስጥም ጭምር ነበር።
በቀደምት ቻይናውያን ፈላስፎች ዘንድ
የቀደምት ቻይናውያን ፍልስፍና በቀድሞው የምስራቁ ዓለም ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮ ያለፈ ነበር። ይህ ተጽዕኖ አሁንም ድረስ በምስራቁም ሆነ በምዕራቡ ዓለም ላይ ይንጸባረቃል። ምሁራዊ አመለካከቶችን ብቻ ሳይሆን ፖለቲካን፣ ማህበረሰብን እና ባህልን ቀርጿል። በዘመኑም በርካታ የፍልስፍና አመለካከቶች ተነስተዋል። እያንዳንዱም በአስተዳደር፣ በስነምግባር፣ በሰው ተፈጥሮ እና በህዋ አካላት ላይ ልዩ ልዩ አመለካከቶችን አበርክቷል። ለምሳሌ ያህልም ኮንፊሽየሳዊነት (Confucianism)፣ ህገኝነት (Legalism)፣ ዳኦዊነት (Taoism) የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው። በእነዚህ ፍልስፍናዎች ውስጥ፣ ዓለም በሂደትና በለውጥ ውስጥ እንደምትገኝ የሚያመላክቱ ሐሳቦች ይንጸባረቁ ነበር።
በዘመናችን በሳይንሱ በሥነ ፈለክ ጥናት ዘርፍ (ኮስሞሎጂ)፣ ያለንበት ሕዋ አመጣጥ ሲተነትኑ አስቀድሞ በታላቅ ፍንዳታ (Big Bang) እንደጀመረ ይናገራሉ። ይህ ጽንሰ ሐሳብ የሚያብራራው፣ ከዚህ ፍንዳታ በፊት እጅግ በጣም ከፍተኛ በሆነ የስበት ኃይል የታጨቀ፣ ወርድም ሆነ ስፋት ወይም ርዝማኔ የሌለው ‘ነገር’ (initial singularity) እንደነበር ነው። ከዚህ በስበት ከታጨቀው ነገር በፊት ምን ነበር ለሚለው ጥያቄ፣ የሚሰጠው መልስ በአብዛኛው ‘ምንም/ባዶ’ ነበር ሲሉ ይገልጻሉ።
ይህ የዘመናዊው ኮስሞሎጂ ትንታኔ፣ የዓለምን አመጣጥ በተመለከተ በጥንታዊ ፍልስፍናዎች ከነበሩት ‘ከባዶ መፈጠር’ ወይም ‘ከአንድ ምንጭ መብቀል’ ከሚሉ አስተሳሰቦች ጋር አንዳንድ የሐሳብ ቅብብሎሽ እንዳለው ማየት ይቻላል።
በመሠረቱ ወርድም፣ ስፋትም፣ ርዝመትም የሌለው ነገር በራሱ አደናጋሪ እንዲሁም የቁሳዊውን ዓለም መሠረታዊ ሕግጋት ያልተከተለ ወይም የጣሰ ምናባዊ አገላለጽ ነው። ምክንያቱም የስበት ኃይል ይኖር ዘንድ ክብደት ያለው ነገር ሊኖር ይገባል። ክብደት ያለው ነገር ሲኖር ደግሞ ወርድ፣ ስፋት እንዲሁም ርዝማኔ ሊኖረው ግድ ነው።
ይህ አባባል “Initial Singularity” (የጅማሬ ነጥብ) በሚለው የቢግ ባንግ ጽንሰ ሐሳብ ላይ የሚነሳውን ትልቅ የፍልስፍና እና የፊዚክስ ጥያቄ በጥሩ ሁኔታ ያሳያል።
ይሁንና አጽናፈ ዓለሙ ከ’ምንም/ባዶ’ ነገር ሊወጣ እንደሚችል ከጠቆሙት የኳንተም ኮስሞሎጂስቶች መካከል አንዱ የዩክሬናዊው ሳይንቲስት አሌክሳንደር ቪለንኪን ነበር።
በሚያስደንቅ መልኩ፣ ዛሬ እንደ ሳይንሳዊ ትንተና ተብሎ በሳይንስ ጆርናሎች ላይ ለመለጠፍ የበቃው ይህ የሕዋ (አጽናፈ ዓለም) አመጣጥ ጽንሰ ሐሳብ (በተለይም ከምንም/ነጠላ ነጥብ መጀመሩ)፣ አስቀድሞ በቻይና የዳኦዊነት (Taoism) ፍልስፍና ውስጥ የነበረ ትምህርት ነው።
ይህንን ጉዳይ ኢልዛ ቬይት በ**“Evolution in the Far East”** በሚለው ጽሑፋቸው ሲያስረዱ እንዲህ ብለዋል፦
“ከምዕራቡ ዓለም በተነጻጻሪ መልኩ፣ የሩቅ ምስራቅ ፈላስፋዎች ስለ ሥነ-ሕይወት አመጣጥ በዝግመተ ለውጥ ነጥቦች መሠረት ያስረዱ ነበር። በጣም የሚገርመው የዚያን ዘመን ፈላስፋዎች የፍጥረትንም ሆነ የሕዋን አነሳስ ከፍጥረት በላይ በሆነ ፈጣሪ ወይም ነዳፊ/ንድፍ አውጪ ጋር አለማያያዛቸው ነበር።”2
በተጨማሪም
“ ከመጀመርያው ጀምሮ የቻይና ፈላስፋዎች በፍጥረት ላይ ከሌላው በጣም የተለየ አመለካከት ነበራቸው። ከእነዚህ መካከለም ህዋ በራሱ የተፈጥሮ ሂደት አሁን ወዳለበት ደረጃ እንደ ደረሰ. . .”2
በተለይ የታኦዊነት ፍልስፍናን ስንመለከት አስገራሚ የሆኑ ተመሳሳይ ነጥቦችን እናገኝበታለን። ዳኦዊነት(ታኦዊነት) ፍልስፍናም ሐይማኖትም ሲሆን አስተምሮቱ ከ ክርስቶስ ልደት በፊት በ 400 ዓመተ ዓለም አካባቢ እንደተነሳ ብዙዎች ይስማሙበታል።
ታኦዋዊያን ስለ ሕዋ አነሳስ ጅማሬ ሲያስረዱም
“በታኦዋዊ/ዳኦዋዊ ፍልስፍና መሰረት ‘ባዶ/ምንም’ ለፍጥረታት ጅማሬና ሕልውናን የሰጠ ነው።”3
ይህ ዛሬ ላይ ከ ’ጅማሬ ነጥብ’ በፊት ‘ምንም ነገር’ ነበር የሚለው ትንታኔ ቀድሞውኑም የፓንቴይዝም ሐይማኖት እና ፍልስፍና በሆነው በ ታኦ ትምህርት ውስጥ ነበር።
ይህ ብቻ ሳይሆን ከዚህ የ’ጅማሬ ነጥብ’ ተብሎ ከተጠቀሰው ነገር በታላቅ ፍንዳታ የሕዋ አካላት እንድተገኙ በተመሳሳይ መልኩ በታኦዋዊያን ፍልስፍና መሰረት ሰማይና ምድር በ አንድ ትርምሳዊ ሀይል በሞላው ህዋዊ(ሕዋን የሚያስገኝ) ‘ዕንቁላል’ ውስጥ እንደነበሩ ከዚያም ከጊዜያት በኋላ እንደተለዩ ያስተምራሉ።
[የፓ’ንኩ ታሪክ የሚያትተው] “ሰማይና ምድር በ አንድ የትርምስ ቀውስ እንቁላል ውስጥ ነበሩ። ከ 18 ሺህ ዓመታት በኋላም ይህ የትርምስ ቀውስ እንቁላል ሲበታተን ወደ ላይ ከፍያለው ሰማይ ሲሆን ጨለማማ እና ጭጋጋማ የሆነው ደግሞ ምድር ሆነ።”4
ዛሬ ላይ በተለያዩ የትምህርት ተቋማት ስለ ሥነ-ፍጥረታት በተለይም እና ህዋ አካላት መነሻ በየደረጃው የሚሰጠው የሳይንስ ትንተና ከዚህ አስተሳሰብ ጋር ይመሳሰላል።
የዚህ መጽሐፍ ማዕከል ወደሆነው ወደዳርዊንያን ዝግመተ ለውጥ ጽነሰ ሀሳብ ስንመጣ አሁንም ቀደምት ቻይናውያን ይህ አስተሳሰብ የፍልስፍናቸው አንዱ አንጓ ነበር።
“ሩቅ ምስራቅ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረውን የቀደምት ቻይናውያንን አስተሳሰብ ስንቃኝ ባሁን ዘመን በምዕራቡ ዓለም ጋር ካለው የዳርዊንያን አመለካከት ጋር ተመሳሳይነት አለው።”5
ይህ የቁሳዊ ፍልስፍና ትንተና ከዳርዊንም ሆነ ከዘመናዊው ሳይንስ 2500 ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲንጸባረቅ የነበረ ሐሳብ ነው።
በታኦዊነት ፍልስፍና ውስጥ፣ የመላመድ (Adaptation) እና የዝግመተ ለውጥ (Evolution) ጽንሰ-ሐሳብ ከታኦ (Tao) ማዕከላዊ ሀሳብ ጋር በጥልቅ የተሳሰረ ነው።
ታኦ ያለማቋረጥ በዝግመታዊ ለውጥ ሂደት ላይ ያለውን የአጽናፈ ዓለም ተፈጥሮአዊ ስርዓትን ይወክላል። በዚህም ምክንያት ታኦዊያን ከዚህ ስርዓት ጋር ተሰናስኖ ለመኖር በዚህ ዝግመታዊ ለውጥ ሂደት ውስጥ መሆን አማራጭ የሌለው እንደሆነ ያስረዳሉ።
ይህ ማለት፣ ታኦዊነት ዓለምን እንደ ቋሚና የማይለዋወጥ ነገር አድርጎ አያይም። ይልቁንም፣ ሁሉም ነገር በቋሚ እንቅስቃሴ፣ ለውጥና መላመድ ውስጥ እንዳለ ያምናል። በዚህ ተለዋዋጭ ስርዓት ውስጥ፣ ፍጥረታትም ሆኑ ክስተቶች ከታኦ ፍሰት ጋር ተስማምተው ለመኖር የማያቋርጥ መላመድ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ያስተምራል።
ይህ የተፈጥሮ ስርዓት ራሱን ይበልጥ ወደ ተሻለ ስርዓት ለመቀየር በማያቋርጥ ሂደት ላይ ስለሆነ ጣልቃ መግባት ወይም መቃረን አያስፈልግም ሲሉ ይናገራሉ።
ይህ አስተሳሰብ በዳርዊን ከተገለጸው ‘Survival of the Fittest’ ተብሎ ከተጠቀለለው መሰረታዊ አስተሳሰብ ጋር ፍጹም አንድ አይነት ነው።
ልክ ታኦዋዊያን የተፈጥሮ ስርዓት [ታኦ] ራሱን በማሻሻል ሂደት ላይ ስለሆነ ጣልቃ መግባት አያስፈልግም ብለው ያስተምሩ እንደነበር ዳርዊን ተፈጥሮ በራሷ ልታስወግዳቸው የፈለገችውን ደካማ ፣ታማሚ እና ችግረኛ ማህበረስቦችን በህይወት እንዲቆዩ መርዳት ያንን የተፈጥሮ ህግ መጣስ አግባብ አይደለም ሲል ተናግሯል።
የዝግመተ ለውጥ አስተሳሰብ በቀደምት ግሪካውያን ፈላስፎች ዘንድ
የዝግመተ ለውጥ አስተሳሰብ፣ በተለይም ዝርያዎች በረዥም ጊዜ ውስጥ በሂደት ይለወጣሉ የሚለው አመለካከት፣ በጥንት ቱርክ እና ግሪካውያንም ዘንድ ተመሳሳይ መሰረት ባለው ፍልስፍና በስፋት ይነገር ነበር። ዛሬ በዓለማችን ላይ፣ በተለይም በምዕራቡ ዓለም፣ ተንሰራፍቶ ያለው የዝግመተ ለውጥ ‘ፍልስፍና’ መነሻውን በዚያን ጊዜ በጥንታዊ ግሪክ ፍልስፍናዎች ውስጥ ማየት እንችላለን።
የግሪካውያን ፍልስፍና አይሎ በነበረበት ዘመናት፣ የፍልስፍና አስተማሪዎች በከፈቱት ትምህርት ቤት ውስጥ ከፍልስፍናቸው መካከል ስለ ሥነ-ፍጥረት አመጣጥ እና የሕዋ አጀማመር ትምህርቶችን ያስተምሩ ነበር። ከእነዚህ የትምህርት ማዕከሎች ተጠቃሽ ከሆኑት ውስጥ ሚሌዥያን ትምህርት ቤት (Milesian School) አንዱ ሲሆን፣ የተከፈተው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ6ኛው ክፍለ ዘመን ነበር።
ሕይወት አልባ ከሆነ አካል ሕይወት መምጣት (Abiogenesis)
አናክሲማንደር (Anaximander) (ከ610-546 ዓ.ዓ ገደማ የኖረው): አናክሲማንደር ሕይወት የተነሳው ሕይወት ከሌለው ጭቃ መሰል ነገር እንደሆነ ያስረዳ ነበር። ይህ ሐሳብ በዘመናችን ሳይንስ ውስጥ አባዮጀነሲስ (Abiogenesis) በሚለው ትንተና ውስጥ ከሚጠቀሰው “ሾርባ መሰል ነገር” (primordial soup) ጽንሰ-ሐሳብ ጋር ይመሳሰላል። አናክሲማንደር ሕይወት ከኩሬ አጠገብ እንደተነሳ ሲናገር፣ አባዮጀነሲስም ሕይወት ከውሃማ አካላት እንደተነሳ ያስረዳል።
“አናክሲማንደር እንዳለው የመጀመሪያዎቹ ሕያዋን ፍጥረታት እርጥበት ባለው ጭቃማ ነገር ውስጥ ተወልደው በእሾህ ቅርፊት ተዘግተው እድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ ወደ ደረቅ ክፍል እንደ ወጡ እና ቅርፊቱ ከወደቀ በኋላ ለአጭር ጊዜ የተለየ [የተቀየረ] ማንነት ይዘው ይኖሩ ነበር።”6
ቴልስ (Thales of Miletus) (ከ620-546 ዓ.ዓ ገደማ የኖረው): ቴልስ ሰዎች ከእንስሳት፣ እንስሳት ከዕፅዋት፣ ዕፅዋት ደግሞ ከሕይወት ከሌለው አካል በሂደት እንደመጡ ሲያስተምር፣ ለሁሉም መነሻ የውሃ አካል እንደነበር ያምን ነበር። ይህ ደግሞ ሕይወት አልባ ከሆነ ነገር የመነጨ መሆኑን ያመለክታል።
የዝግመተ ለውጥ ሂደት አስተሳሰብ
ቴልስ (Thales of Miletus) እና አናክሲማንደር (Anaximander) : እነዚህ ፈላስፎች ሰዎች ከእንስሳት፣ እንስሳት ደግሞ ከዕፅዋት፣ ዕፅዋት ደግሞ ከሕይወት ከሌለው አካል በዝግመተ ለውጥ እንደመጡ ያስተምሩ ነበር።
ዜኖፌንስ (Xenophanes) (ከ570-478 ዓ.ዓ ገደማ የኖረው): ዜኖፌንስ በደረቅ መሬት የሚመላለሱ እንስሳት በውሃ አካላት ውስጥ ከሚኖሩ እንስሳት በዝግመተ ለውጥ ሂደት እንደተገኙ ያስተምር ነበር። ለዚህም እንደ ማስረጃ የሼል ቅሪተ አካል በተራሮች ጫፍ ላይ መገኘቱን ይጠቅሳል።
ሄራክሊተስ (Heraclitus of Ephesus) (ከ535-475 ዓ.ዓ ገደማ የኖረው) [1]: ሄራክሊተስ ሥነ ፍጥረት በማያቋርጥ የለውጥ ሂደት ላይ እንዳለ ያስረዳል። እሱም አጽናፈ ዓለሙ ጅማሬም ሆነ ፍጻሜ እንደሌለው እንዲሁም ለዘላለም ሲካሄድ የነበረ ያልተቋረጠ ሂደት አሁን ያሉትን ፍጥረታት እንዳስገኘ ያስተምር ነበር።
ይህ የዘመኑ የሳይንስ ውጤት ከተባለው የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ፣ በመሠረታዊ ሐሳቦቹ የሚስማማ ሆኖ እናገኘዋለን።
የተፈጥሮ ምርጫ እና የዘፈቀደ ለውጦች
ኢምፔዶክልስ (Empedocles) (ከ484-424 ዓ.ዓ ገደማ የኖረው): ኢምፔዶክልስ የሁሉም ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት የአካል ክፍሎች በተናጠል ወይም ለብቻቸው በሂደት የተገኙ እና በዘፈቀደ ጥምረት የተሰባሰቡ እንደሆኑ ያምን ነበር። ከዚህም በላይ፣ ለኑሮ አላስፈላጊ የሆኑ እና የማይመጥኑ ጥምረቶች ከጊዜያት በኋላ ሲጠፉ፣ ተስማሚ እና ጠንካራ የሆኑት ግን ቀጥለዋል ሲል ያስተምራል። ይህ ሐሳብ ከዳርዊን “የበቁቱ ይኖራሉ” (Survival of the fittest) [3] ከሚለው አስተሳሰብ ጋር እጅግ ይመሳሰላል።
ሉክሪቲየስ (Lucretius) (ከ99-55 ዓ.ዓ ገደማ የኖረው) : ልክ እንደ ኢምፔዶክልስ፣ ሉክሪቲየስም ተመሳሳይ የሆነ የዝግመተ ለውጥ ትንታኔ ሲያስተምር፣ የተፈጥሮ ምርጫ አንዳንድ እንስሳትን ከምድር ገጽ እንዳጠፋች ያስተምር ነበር።
ይህ በሚያስገርም መልኩ ከዳርዊን “የበቁቱ ይኖራሉ” (Survival of the fittest) ከሚለው አስተሳሰብ ጋር አንድ አይነት ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ የዘመናዊ ሳይንስ ግኝት የተባለው፣ ከዳርዊን 2000 ዓመታት በፊት የነበረ በፍልስፍናው ዓለም ተጽእኖ ያሳደረ አስተሳሰብ ነበር።
ምንም እንኳን በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ሥነ ፍጥረትን ከፈጣሪ አልባነት አንጻር ለማስረዳት የሚደረግ ፍልስፍና ነባር የሆነ ጥረት እና አስተሳሰብ ቢሆንም በ አንጻሩ ደግሞ በፈጣሪ የበላይነት እና ፍጥረት አስጀማሪነት የነበረ አስተሳሰብ እና ልምምድ ደግሞ ከዚያም ቀደም ሲል የነበረ ነገር ነው።
“በዚያም ዘመን ሰዎች የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም መጥራት ጀመሩ።”7
በመሆኑም የዝግመተ ለውጥ ጽነሰ ሐሳብም ሆነ የሕዋ አመጣጥ ትንታኔዎች እንደሚባለው የዘመኑ የሳይንስ ቱሩፋቶች ሳይሆን ቀድሞም የነበረ ፍልስፍና ነበር።
ማጣቀሻዎች:-
1. Ilza Veith P.H.D, Evolution in the Far East, Perspectives in Biology and Medicine, Summer 1960 page 528
2. Ilza Veith, “ Creation and Evolution in the Far East” p.2
3. David L. Johnson, A Reasoned Look at Asian Religions.
4. David C. Yu, The Creation Myth and Its Symbolism in Classical Taoism, oct 1981, page 485
5. David C. Yu, The Creation Myth and Its Symbolism in Classical Taoism, oct 1981, page 479
6. Ilza Veith P.H.D, Evolution in the Far East, Perspectives in Biology and Medicine, Summer 1960 page 528
7. ዘፍ 4፥24

