የሽግግራዊ ቅሪተ አካል ምንድነው?
ሽግግራዊ ቅሪተ አካል ማለት በዝግመተ ለውጥ ሂደት ውስጥ አንድ ዓይነት ፍጡር (ዝርያ) ወደ ሌላ ዓይነት ፍጡርነት ሲለወጥ የነበረውን ቀስ በቀስ የሚደረግ ለውጥ የሚያሳይ ፍጡር ቅሪት ማለት ነው። እነዚህ ቅሪተ አካላት ሁለት የተለያዩ የፍጡር አይነቶች (ለምሳሌ፡ ከዓሳ ወደ አምፊቢያን ወይም ከሚሳቡ እንስሳት ወደ አጥቢ እንስሳት) መካከል ያሉትን መካከለኛ (Intermediary) ባህሪያት ይዘው ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ለምሳሌ እንደ ዝግመተ ለውጥ ተቀባይ ሳይንቲስቶች ትንታኔ መሰረት አሁን ያሉ የወፍ ዝርያዎች ቀድሞ ከነበሩ ዳይኖስሮች በለውጥ የመጡ እንደሆነ ይናገራሉ። ዳይኖስሩ ወደ ወፍ ፍጥረትነት እስኪቀየር ድረስ በመካከል ያሉ ፍጥረታት የሽግግር ፍጥረታት ይባላሉ።
የዳርዊን ጽንሰ ሐሳብ እና የቅሪተ አካላት ክፍተት
ቻርልስ ዳርዊን በ19ኛው ክፍለ ዘመን የ “የተፈጥሮ ምርጫ” ጽንሰ ሐሳብን ይዞ ሲመጣ፣ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ ከ”ጋራ ነባር ቅድመ አያት” እንደመጡ አብራርቷል። ይህ ሐሳብ ትክክል ከሆነ፣ የቅሪተ አካል መዛግብት (Fossil Record) አንድ ዝርያ ቀስ በቀስ ወደ ሌላ ዝርያ ሲሸጋገር የሚያሳዩ እጅግ በርካታ የሽግግር ቅሪተ አካላትን መያዝ ነበረባቸው።
በወቅቱ የዳርዊን ችግርና ምላሽ
ምንም እንኳን ዳርዊን ይህን “የጋራ ነባር ቅድመ አያት” የሚል ሀሳብ ይዞ ቢመጣም፣ ለዚህ እንደ ማስረጃ ሊሆን የሚችል ቀጥተኛ የቅሪተ አካል ማስረጃ ግን ሊያቀርብ አልቻለም። በተለይም በመጽሐፉ ምዕራፍ 10 እና 11 ላይ፣ እነዚህ የሚጠበቁ የነበሩ የቅሪተ አካል ዓይነቶች (ማለትም፣ አንድ ዝርያ ወደ ሌላ ዝርያ ሲለወጥ ያለውን ቀስ በቀስ ሽግግር የሚያሳዩ ቅሪተ አካላት) ያልተገኙበትን ምክንያት ሲገልጽ፣ በወቅቱ የነበሩ ፓሊዮንቶሎጂስቶችና ጂኦሎጂስቶች በቂ ምርምር ስላላደረጉ ነው የሚል ነበር። አክሎም፣ ወደፊት ብዙም ሳይርቅ የወደፊት የዘርፉ ተመራማሪዎች እነዚህን ቅሪተ አካላት እንደሚያገኙ የተስፋ ቃል ሰጥቶ ነበር።
ከ160 ዓመታት በኋላ ያለው እውነታ
ምንም እንኳን ዳርዊን ይህን መጽሐፍ ከጻፈ ከ160 ዓመታት በላይ ቢቆጠሩም፣ እነዚህ የሽግግር ቅሪተ አካላት እንደተጠበቀው በብዛትና በቀጣይነት አልተገኙም። በቅሪተ አካል መዛግብት ውስጥ ዝርያዎች በድንገት ብቅ ሲሉ እና ብዙም ሳይለወጡ ለረጅም ጊዜ ሲቆዩ መታየቱ፣ የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብን የሚተቹ ተመራማሪዎች ከሚያነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች አንዱ ነው።
ይህ “የመዛግብት ክፍተት” ተብሎ የሚታወቀው ሁኔታ፣ በዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ መሰረት የሚጠበቀውን ቀጣይነት ያለው የዝርያዎች ሽግግር ሙሉ በሙሉ አያሳይም። ይህ ችግር የዝግመተ ለውጥ ሂደት ቀስ በቀስና ቀጣይነት ያለው ሳይሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ድንገተኛ ለውጦች ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚያስቀምጠውን የ”Punctuated Equilibrium” ጽንሰ ሐሳብን (በስቲቨን ጄይ ጉልድ እና ናይልስ ኤልድሪጅ የቀረበ) የመሰሉ አማራጭ ማብራሪያዎችን አስከትሏል። ይህ ደግሞ የዝግመተ ለውጥን ፍጥነት እና ዘዴ በተመለከተ በሳይንሳዊው ማህበረሰብ ውስጥ ውይይቶችን እያስነሳ ይገኛል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ የዘመናችን የፓሊዮንቶሎጂስት ሊቅ የሆኑት ስቴቨን ስታንሊይ የቅሪተ አካል ስብስቦቻችንን በመመልከት ይህን በመጽሐፋቸው አስፍረዋል፦
“…አብዛኞቹ የቅሪተ አካል ተመራማሪዎች፣ በተመዘገቡት የቅሪተ አካል ዝርያዎች መካከል ሽግግራዊ ቅርጾች የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የሌለባቸው፤ ክፍተቶች ብቻ ያሉበት ሁኔታ ገጥሟቸዋል” [2]
ለችግሩ የቀረቡ አማራጭ ማብራሪያዎች
ይህ “የመዛግብት ክፍተት” (Gaps in the Fossil Record) በሳይንሳዊው ማህበረሰብ ውስጥ ትልቅ ውይይት አስነስቷል።
የፓሊዮንቶሎጂስቶች የሆኑት ስቲቨን ጄይ ጉልድ እና ናይልስ ኤልድሪጅ ይህንን ክፍተት ለመመለስ “ፐንክቹዌትድ ኢኪዊሊብሪየም” የተባለ ጽንሰ ሐሳብ አቅርበዋል። ይህ ሐሳብ የዝግመተ ለውጥ ሂደት ቀስ በቀስና ቀጣይነት ያለው ሳይሆን፣ ዝርያዎች ለአጭር ጊዜ በድንገትና በፍጥነት ከተቀየሩ በኋላ ለረጅም ጊዜ ሳይለወጡ እንደሚቆዩ ያስቀምጣል። ይህ ደግሞ በዝግመተ ለውጥ ፍጥነትና ዘዴ ላይ ያለውን የዳርዊንን መሠረታዊ ግምት የሚገዳደር ሆኗል።
ታዋቂው ፓሊዮንቶሎጂስት ስቴቨን ስታንሊይ ይህንን ችግር ሲያጠቃልሉት፦
“የቅሪተ አካል ስብስቦቻችንን ስንመለከት አዲስ የፍጥረት አይነትን የሚያስገኝ የዝግመተ ለውጥ ሂደት የሚያመላክት አንድም ምሳሌ የለም”[1]
ብለዋል።
በዚህም ምክንያት፣ የዳርዊንን ሐሳቦች ከዘመናዊ የዘረመል ግኝቶች ጋር ለማዋሃድ የሚሞክሩ የኒዮ-ዳርዊኒያን ተመራማሪዎች፣ አዲስ ዝርያዎችን የመፍጠር ሂደትን ለማስረዳት እንደ የዘረመል መንሸራተት (Genetic Drift) እና የዘረመል መለወጥ (Mutation) የመሳሰሉ ተጨማሪ መንገዶችን በዳርዊን ትንተና ላይ ለመጨመር ተገደዋል።
ይህ የሚያሳየው፣ የአዳዲስ ዝርያዎች አመጣጥ በተመለከተ አሁንም ድረስ በሳይንሳዊው ማህበረሰብ ውስጥ ክርክርና ምርምር የሚያስፈልጋቸው ብዙ ክፍተቶች እና ጥያቄዎች እንዳሉ ነው።
የብራዚል ባዮሎጂክ ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ዳግላስ አክስ ይህንን አጣብቂኝ ሲገልጹ፦
“በዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ዘዴዎች የተራቀቁ አዳዲስ ሕይወት ያለው ነገር (ባዮሎጂያዊ) ባህሪያትን መፍጠር የቻለ አንድም ሳይንቲስት የለም፣ ይህ ደግሞ ሁሉም ሳይንቲስቶች የንድፈ ሃሳቡን ትክክለኛነት እንዲጠራጠሩ ሊያደርግ ይገባል።” [3]
ብለዋል።
ማጣቀሻዎች
1.ስቴቨን ስታንሊይ፣ ፓለንቲዮሎጂስት “Macroevolution: Pattern and Process” p 39
2.Leslie E. Orgel, “The Origin of Life on the Earth,” Scientific American (vol. 271, October 1994), p. 83.
3. Axe, D. (2016). Undeniable: How biology confirms our intuition that life is designed. HarperOne.

