ዳርዊኒዝም እና የማህበራዊ የበላይነት ፍልስፍና : የሔሬሮ ሕዝብ ላይ የዘር ጭፍጨፋ

ሶሻል ዳርዊኒዝም በቻርለስ ዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ (“ለመኖር የሚደረግ ትግል” እና “የተፈጥሮ ምርጫ”) ላይ የተመሠረተ የፍልስፍና አስተሳሰብ ነው። በማኅበረሰቦችና በዘሮች መካከል የሚደረጉ ግጭቶች እና ጦርነቶች እንደ ተፈጥሮአዊ የዕድገት መንገድ የሚቆጠር ሲሆን፣ “ብርቱዎችና የሰለጠኑት” (በዝግመተ ለውጥ የላቀ ደረጃ ላይ ያሉ) ደካማ የሆኑትን ማኅበረሰቦች በመደምሰስ ወይም በመግዛት የሰው ዘርን ያሻሽላሉ የሚል እምነት ነው። ይህ አስተሳሰብ የሰውን ልጅ ክብርና ዋጋ ያሳንሳል በሚባለው የዝግመተ ለውጥ ትምህርት ምክንያት የመጡ አደገኛ አስተሳሰቦችን ያሳያል የተባለው የሶሻል ዳርዊኒዝም የፍልስፍና ትርጓሜ፣ በዓለም ታሪክ ውስጥ ለብዙ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች መንስኤ ሆኗል።

የሰው ልጅን ክቡርና እኩል ፍጡር አድርጎ ከሚመለከተው የፍጥረት መሠረተ እምነት በተቃራኒ፣ የዳርዊን ፍልስፍና የሰዎችን ዋጋ በዝግመተ ለውጥ ደረጃ በመመዘን፣ ጭካኔ የተሞላበት ዘረኝነትን እንደ ተፈጥሯዊ ክስተት ለማሳየት ሞክሯል።

ቻርለስ ዳርዊን በየካቲት 24 ቀን 1871 ለመጀመሪያ ጊዜ በታተመው “የሰው ልጅ አመጣጥ” (The Descent of Man) በተሰኘው መጽሐፉ፣ የገለጸው የተፈጥሮ አመራረጥ ጽንሰ ሐሳብ በሰው ልጆች ማኅበረሰብ ላይም ሊተገበር እንደሚችል በግልጽ አስፍሯል። ይህ የዝግመተ ለውጥ ትምህርት ወደ ተግባር የመተርጎም አደገኛ ጅማሮ ነበር። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ፣ ዳርዊን የሰለጠኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ችግረኛ የሆኑትን በመርዳት የሰው ልጅ ዘርን ጎድተዋል የሚል አመለካከት ነበረው።

እርሱ እንዳብራራው፣ ተፈጥሮ ራሷ ልታስወግዳቸው የፈለገችውን ደካማ፣ ታማሚ እና ችግረኛ ማኅበረሰቦችን በሕይወት እንዲቆዩ መርዳት የተፈጥሮን ሕግ መጣስ ነው ሲል አስቀምጧል። በዚህም የተነሳ፣ ዳርዊን እንዲህ አይነቱ የድጋፍ እና የእርዳታ ሰብዓዊ አገልግሎቶች ደካማው ዘር ዝርያው እንዲቀጥልና የተሻለውን ዘር እንዲበክል ሊያደርግ ስለሚችል ቀስ በቀስ የሰውን ዘር ከምድረ ገጽ ሊያጠፋው ይችላል ብሎ አምኖ ነበር። በተቃራኒው ደግሞ ሌላ አማራጭ የሚመስል ትንተና ሲሰጥ ደግሞ፣ ወደፊት ብርቱ የሆኑት የማኅበረሰብ ክፍሎች ደካማ የሆነውን ማኅበረሰብ ከምድረ ገጽ ያጠፋሉ ሲል ተናግሯል።

 

“ወደፊት ብዙም ሳይርቅ የሰለጠነው የሰው ልጅ ማህበረሰብ ደካማ እና እንስሳዊ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ከምድረገጽ እንደሚያጠፋ እና እንደሚተካቸው እርግጠኛ ነኝ” [1]

ይህ አባባል፣ የዝግመተ ለውጥ አስተሳሰብ ወደ ፍልስፍና ሲተረጎም ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ በግልጽ ያሳያል። ምንም እንኳን ዳርዊን ይህ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል በመገንዘቡ የመወዛገብ ስሜት ቢሰማውም፣ የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ መሰረት ያደረገው ይህ አስተሳሰብ በጀርመን የተነሱ አዳዲስ ፖለቲከኞችንና ሳይንቲስቶችን የሐሳብ ፍልስፍና መሠረት ጥሏል።

ዳርዊኒዝም ለጥፋት ርዕዮተ ዓለሞች እንደ መሠረት

ይህ አዲስ፣ በዝግመተ ለውጥ የተነሳ የመጣ እውቀት፣ ወደፊት የበላይነትን ለማስገኘት ለሚደረጉ ማንኛውም ድርጊቶች—እንደ ጦርነት፣ ግድያ፣ መሬት ወረራ፣ ቅኝ ግዛት እና የመሳሰሉት—እንደ ሥነ ሕይወት መሠረት ተቀባይነት ያለው መሆኑን የሚያረጋግጥ አስተሳሰብ ነበር። የሰው ልጅ ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል እንደተፈጠረ እና እኩል ዋጋ እንዳለው የሚገልጸውን ለዘመናት የቆየውን አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ የሻረ አመለካከት ነበር።

ፕሮፌሰር ሪቻርድ ዊካርት (ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ) እንዳብራሩት፣

“በወቅቱ የነበሩትን ሳይንቲስቶች ስንመለከት በአብዛኛው በሚባል ደረጃ ዘረኝነትን፣ ዘር የማጽዳት ተግባርን እንዲሁም የሌሎችን መሬት እና ሀብት መቀማትን የሚደግፉና የሚያበረታቱ ነበሩ”። [1]

በሌላም በኩል የጀርመን ዚኦሎጂስት ጉስታቭ ፌይገር (1870)

“የመጠፋፋት ጦርነት . . . የተፈጥሮ ህግ ነው . . . ህይወት ያላቸው ፍጥረታትም እስካሁን ሊቀጥሉ የቻሉት በዚሁ ነው ” [1]

ሲል ገልጿል።

በተመሳሳይ መልኩ፣ የጀርመን ኢትኖሎጂስት ፍሬድሪክ ሄልዋልድ (1875) 

“ለመኖር የሚደረግ ትግል ለዝግመተ ለውጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ሁሉ . . . በሰው ልጅም ታሪክ የደካማ ህዝቦች በሰለጠኑ ሕዝቦች መደምሰስ አንዱ የለውጥ ባህርይ ነው” ብሏል [1]።

የጀርመን የስነ ሕይወት ተመራማሪ ሄይንሪክ ዚግለርም በ1893 ዓ.ም. “Naturwissenschaft” በተባለው ጽሑፉ ላይ

“እንደ ዳርዊን ጽንሰ ሐሳብ መሠረት ከሆነ፣ ጦርነት ለሰው ዘር ዕድገት ከፍተኛ ሚና አለው። ይህም ሲባል በ አካል ደካማ የሆነውን፣ ደካማ አስተሳሰብ ያለውን እና በሞራል ያነሰውን ለሰለጠነውና ለጠንካራው ማህበረሰብ ቦታ መልቀቅ አለባቸው”

በማለት አስቀምጧል። እነዚህ አስተሳሰቦች ሁሉ የሰው ልጆችን ዋጋና ክብር የማሳነስ ውጤቶች ናቸው።

ሶሻል ዳርዊኒዝም በተግባር፡ በናሚቢያ የሄሬሮ ዘር ጭፍጨፋ [2] 

እነዚህ ሁሉ የተወለዱት ከዝግመተ ለውጥ ትምህርት የሆነው ዳርዊኒያዊ አስተሳሰቦች፣ በሶሻል ዳርዊኒዝም ስም፣ በወቅቱ በዝግመተ ለውጥ ሂደት ውስጥ “በዝቅተኛ የለውጥ ደረጃ ላይ የሚገኙት” ተብለው በሚታሰቡት የሰው ዘሮች ላይ ጦርነትና ቅኝ ግዛትን አበረታተዋል። በአፍሪካ በሚኖሩ ማኅበረሰቦች ላይ የተደረገው ጭካኔ የተሞላበት ተግባርም የዚህ አስተሳሰብ ቀጥተኛ ውጤት ነው።

ከ1904 እስከ 1908 ድረስ፣ የጀርመን ጦር ሠራዊት በአካባቢው ይኖሩ የነበሩትን ሄሬሮ የተባሉ ማኅበረሰቦችን ከደቡብ ምዕራብ አፍሪካ ምድር ለማጥፋት ሞክሮ ነበር። አንዳንድ የታሪክ ሊቆችም ይህንን ክስተት የ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያው ዘር ጭፍጨፋ ሲሉ ይኮንኑታል።

በጥቅምት 2, 1904፣ ጀነራል ሎታር ቮን ትሮዛ የዘር ማጥፋት ሥራውን አስጀመረ።የሰጣቸው ምርጫ ቢኖር አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ አልያም ግድያ እንደሚጠብቃቸው ነበር። የሄሬሮ ወንዶች ሲገደሉባቸው፣ ሴቶችና ሕፃናትን ደግሞ በአካባቢው ባለው አሸዋማ በረሃ ለጥም እና ለረሃብ አሳልፎ ሰጣቸው። ጀነራል ቮን ትሮዛ ይህንን ምግባሩን በሶሻል ዳርዊኒዝም አማካኝነት ተቀባይነት ያለው መሆኑን ደጋግሞ ያስረዳ ነበር። በወቅቱ ለነበረ ጋዜጣም፣ የሰው ልጅ ለደካማው ያለ ርህራሄ የዳርዊንን “ለመኖር የሚደረግ ትግል” የሚለውን ሕግ ሊያስቀር አይችልም ሲል ተናግሯል።

በኋላም በጀርመን ከ አንዳንድ ማኅበረሰብ ክፍሎች ተቃውሞ ሲደርስበትም ይህንን ተግባሩን በሌላ መንገድ ቀጠለ። በቀጥታ ከመግደል ይልቅ ወደ ማጎሪያ ማዕከል በማስገባት በበሽታ እንዲያልቁ አደረገ። አንዳንዶቹንም ለሕክምና በሕይወት እንዳሉ ይመራመሩባቸው ነበር። ከሞቱት መካከልም የራስ ቅል አጥንታቸውን ወደ ጀርመን በመላክ የዘር ጥናት በሚያጠኑ ተመራማሪዎች ጥናት ይደረግ ነበር።

በ1908፣ 80 በመቶ የሚሆኑ የሄሬሮ ማኅበረሰቦች በዘር ጭፍጨፋው እንዳለቁ ይታመናል።

ይህ ታሪካዊ ክስተት የሚያሳየው፣ የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ወደ ፍልስፍና ሲተረጎም፣ ከሳይንሳዊ ትርጓሜው ባሻገር፣ ለጭካኔ የተሞሉ የዘር የበላይነት እና የዘር ማጽዳት ርዕዮተ ዓለሞች እንዴት መሠረት ሊሆን እንደቻለ ነው። የሰው ልጅ ክብርና ዋጋ ከዝግመተ ለውጥ ደረጃው ጋር ተቆራኝቶ ሲታይ፣ የሞራል እሴቶች በቀላሉ ተጥሰው የዘር ጭፍጨፋን የመሰሉ አሳዛኝ ድርጊቶች ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ይህ ታሪክ በግልጽ ያስተምረናል። የዝግመተ ለውጥ ትምህርት የሰውን ልጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ያሳንሳል!

ማጣቀሻዎች

1. Weikart, R. (2004). From Darwin to Hitler: Evolutionary Ethics, Eugenics, and Racism in Germany. Palgrave Macmillan.

2. Madley, B. (2005). From Africa to Auschwitz: How German South West Africa Incubated Genocide. European Journal of Genocide Studies, 2(1), 164-180.